የሲዳማ ክልል 12 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል በበጀት አመቱ 12 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር መሰብሰብ ተችሏል አለ የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን፡፡
በክልሉ ታማኝ ግብር ከፋይ ብርቱ የልማት አርበኛ ነው በሚል መሪ ሀሳብ ግንባር ቀደም ለሆኑ ግብር ከፋዮች የዕውቅናና የምስጋና መርሀ ግብር እየተካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ደምሴ እሳቱ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ግብርን በወቅቱና በሀቀኝነት መክፈል ሀገራዊ ግዴታ ብቻ ሳይሆን ፍቅርም ነው ብለዋል።
በበጀት አመቱ 15 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ ባለፉት ወራት 12 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል፡፡
በበጀት አመቱ ቀሪ ጊዜያት እቅዱን ለማሟላት በሚከናወኑ ተግባራት ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በመቅደስ አስፋው