መገናኛ ብዙሃን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በመታገዝ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር መስራት ይገባቸዋል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መገናኛ ብዙሃን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በመታገዝ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር መስራት አለባቸው አሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና እሁድ ኤ.አይ ስቱዲዮ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አሰራር ጥበብ ያሰለጠኗቸውን 25 የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባለሙያዎች አስመርቀዋል።
ባለሙያዎቹ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በይዘት ስራዎች ላይ እሴት መጨመር የሚያስችል የጽንሰ ሃሳብና የተግባር ተኮር ስልጠና ወስደዋል።
ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ስልጠናው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚወስድ በመሆኑ ሰልጣኞች የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ሀገርን ለመቀየር የመስራት ሃላፊነት ይጠበቅባቸዋል።
ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር፣ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር፣ የወል ትርክትን ለመፍጠርና ሀገርን ለማበልጸግ የተያዙ ዋና ዋና እቅዶችን ለማሳካት ቴክኖሎጂውን ጥቅም ላይ በመዋል መስራት ይገባል ብለዋል።
ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ ፊልሞችን በማምረት፣ ሌሎች ሙያተኞችን በማሰልጠን፣ ስለ ቴክኖሎጂው ግንዛቤ ለመፍጠር መስራት እንደሚገባቸው ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ቴክኖሎጂውን በመገናኛ ብዙሃን የይዘት ሥራዎች ውስጥ በመጠቀም ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከርና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ማዋል እንደሚገባ በአጽኖኦት አንስተዋል።
የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎችም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ዕውቀት እንዲስፋፋ መስራት እንዳለባቸው በማስገንዘብ፤ ተቋማትን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የማዘመን ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ በበኩላቸው ቴክኖሎጂውን በአግባቡ መጠቀም በድህረ እውነት በሀገር ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ይረዳል ብለዋል።
ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታም አጋዥ መሆኑን ጠቅሰው፤ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የፈጠራ ስራዎችን ለመደገፍ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው ቴክኖሎጂውን በመጠቀም እንደ ሀገር ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ ለመድረስ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ጠቁመው፤ መገናኛ ብዙሃንም ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
ስልጠናው ለይዘትና ሌሎች ሥራዎች ተጨማሪ አቅም በመፍጠር የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው የመገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎች ተናግረዋል።
ሰልጣኞቹ በበኩላቸው ያገኙትን እውቀት የሀገራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚያውሉ አረጋግጠዋል።
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!