ኢትዮጵያ በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ አበረታች እድገት እያስመዘገበች ነው – ጆርዳን
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በሰውሰራሽ አስተውሎትና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መስክ እያስመዘገበችው ያለው እድገት አበረታች ነው አሉ በኢትዮጵያ የጆርዳን አምባሳደር አምጃድ አል ሞውማኒ።
አምባሳደሩ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጉብኝት አድርገዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) የቴክኖሎጂ ልማትን ለማፋጠን እየተከናወኑ ያሉ የቴክኖሎጂ ልማት ሥራዎችን በተመለከተ ለአምባሳደሩ ገለጻ አድርገዋል፡፡
አምባሳደር አምጃድ አል ሞውማኒ በበኩላቸው፥ የኢንስቲትዩቱ ሥራዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፈጠራ ላይ የተመሰረተ ልማትን እውን ለማድረግ ካላቸው አርቆ አሳቢ ራዕይ ጋር የሚስማሙ መሆናቸውን በአድናቆት አንስተዋል።
ሀገራቸው በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ በአቅም ግንባታ እንዲሁም በልምድ ልውውጥ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት አረጋግጠዋል።