ህገወጥ የነዳጅ ግብይት የተበራከተው የመሸጫ ዋጋው ከጎረቤት ሀገራት ያነሰ በመሆኑ ነው – ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)
በኢትዮጵያ ህገወጥ የነዳጅ ግብይት የተበራከተው የመሸጫ ዋጋው ከጎረቤት ሀገራት አንጻር ያነሰ በመሆኑ ነው አሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)።
ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት የተቋማችውን የ11 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል ።
በዚሁ ወቅት የምክር ቤቱ አባላት የነዳጅ ህገ ወጥነትን ለመቆጣጠርና የነዳጅ ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች ላይ ማደያዎችን ለማስፋፋት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡
ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፥ ከ1ሺ 700 በላይ ማደያዎች አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ገልጸው፥ ተገንብተው የተጠናቀቁ ተጨማሪ 250 ማደያዎችን ለመክፈት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች አዳዲስ ማደያዎች እንዲገነቡ ሀገራዊ ማስተር ፕላን እየተዘጋጀ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ሁሉንም የነዳጅ ምርቶች በጅቡቲ ተርሚናል እያስገባች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ 58 የነዳጅ ኩባንያዎችና 5ሺ 427 የነዳጅ ቦቴዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት 3 ነጥብ 9 ቢሊየን ሊትር ነዳጅ መቅረቡን አስታውሰው፥ እየተገባደደ በሚገኘው የ2017 በጀት አመት 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሊትር ቀርቧል ብለዋል።
ይህም ከባለፈው ዓመት የ10 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ላይ ጠቁመዋል፡፡
በሀገሪቱ የሚታየው ህገወጥ የነዳጅ ግብይት ምክንያቱ በቂ አቅርቦት አለመኖርና የኢትዮጵያ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያነሰ መሆኑ ነው ብለዋል።
ሀገሪቱ ካለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ጀምሮ ከጥቅል የነዳጅ ድጎማ በመውጣት ከዓለም ዋጋ ጋር ለማቀራረብ እየሰራች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ ነዳጅ ከጎረቤት አንጻር ሲታይ ቅናሽ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ