Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የስንዴ ልማት ስኬት ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ነው – ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለተቀሩት የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው አሉ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ።

ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በናይጄሪያ አቡጃ እየተካሄደ በሚገኘው 32ኛው የአፍሪኤግዚም ባንክ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በአፍሪካ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማስመዝገብ ብቃት ያለው አመራር መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

አፍሪካ አህጉራዊ የግብርና አብዮት እንደሚያስፈልጋት ጠቁመው፥ ለዚህም ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት ያስመዘገበችው ስኬት ለተቀሩት የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ አድንቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ስንዴን ወደ ውጭ መላክ መቻሏ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ያንን ማድረግ እንደሚችሉ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፥ እንደ አህጉር በሌሎች ሀገራትም ሊስፋፋ የሚገባው ስኬት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካን ዕድገት ለማረጋገጥ የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጥ ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል ያሉም ሲሆን፥ በአህጉሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማስመዝገብ ብቃት ያለው አመራር መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም ነው ኦባሳንጆ ያሰገነዘቡት፡፡

በየደረጃው ያለው አመራር የሚያስተዳድረውን አካባቢ አውቆ በፖሊሲና ስትራቴጂዎች በመታገዝ በብቃት መምራት ከቻለ የአፍሪካን ህዳሴ ለማረጋገጥና የሕዝቡን ሕይወት ለማሻሻል እንደሚቻልም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከስንዴ ተረጂነት ወጥታ ስንዴ ላኪ ለመሆን የበቃችው በልማቱ ላይ ያተኮረ ብቁ አመራር መስጠት በመቻሉ ነው ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል፡፡

የአህጉሪቱ የእርስ በእስር የንግድ ልውውጥ ከሌሎች አህጉራት ጋር ከምታደርገው የንግድ ልውውጥ ያነሰ መሆኑን በማንሳት፥ አህጉራዊ የእርስ በእርስ የንግድ ልውውጥ ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዘብዋል፡፡

ለዚህም በዘመኑ ቴክኖሎጂ በመታገዝና ሌላ ዓለም አቀፍ መገበያያ ሳያስፈልግ መገበያየት የሚቻልበት ሁኔታ መፍጠር ተችሏል ያሉ ሲሆን፥ ለአብነትም ኡጋንዳ በብዛት የምታመርተውን ወተት ከፍተኛ እጥረት ወዳለበት ናይጄሪያ ማቅረብ መጀመሯን አንስተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.