የጎንደር ከተማ 13 ሺህ 200 የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት ወሰነ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጎንደር ከተማ አስተዳደር ለዓመታት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ ለቆየው የህብረት ሥራ ማህበራት የቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል።
የከተማ አስተዳደሩ በየተለያየ ጊዜ ለተደራጁ 550 የራስ አገዝ የመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህበራት የመስሪያ ቦታ ለመስጠት ወስኗል።
የከተማው ከንቲባ ኮሚቴ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎችን መሰረት አድርገዉ ለተደራጁት 13 ሺህ 200 የከተማዋ ነዋሪዎች ነው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት የወሰነው።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸዉ ዳኘዉ እንደገለፁት፤ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ የቆየውን የህብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በህብረት ስራ ማህበራት ለተደራጁ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፤ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የመኖሪያ ቤት ጥያቄውን ለመመለስ የተለያዩ አማራጮችን ተግባራዊ በማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ጥረት እያደረገ ነው ያሉት።
በህብረት ሥራ ማህበራት ለተደራጁ እና አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋም ከ360 ሄክታር መሬት በላይ ዝግጁ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ታደሰ ናቸው፡፡
በምናለ አየነው