Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሐረሪ ክልል የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ ነው አለ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልሉ ምርጫ ጽ/ቤት።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፊታችን ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

ለምርጫው በሁሉም ረገድ የተሟላ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን÷ በዚህ መሰረትም በየምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁስ ተጓጉዞ ተደራሽ እየተደረገ ነው።

በሐረሪ ክልል የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየተሰራጨ መሆኑን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልሉ ምርጫ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ቦጋለ ተናግረዋል።

በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ለድምጽ አሰጣጡ ሒደት መሳካት የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፥ የምርጫ ቁሳቁሶች በመሰራጨት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

የድምጽ መስጫ ወረቀትን ጨምሮ ሌሎችም አስፈላጊ የምርጫ ቁሶች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመሰራጨት ላይ መሆናቸውንና ቦርዱ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ እየሰራ መሆኑን አስተባባሪው ጠቅሰዋል፡፡

የቁሳቁስ ሥርጭቱ በጥንቃቄና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ በጸጥታ ሃይል ታጅቦ እየተጓጓዘ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ተደራሽ እየሆነ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡

በክልሉ በ3 ምርጫ ክልሎች 296 የምርጫ ጣቢያዎች የፊታችን ሰኞ ድምጽ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው ፥ ዜጎች የወሰዱትን ካርድ ዋጋ በመስጠት እንዲወስኑበት ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.