የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣልና የመንግስትን ሚስጥር ለሽብር ቡድን አሳልፎ በመስጠት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል የመንግስትን ሚስጥር በውጭ ላለ የሽብር ቡድን አሳልፎ በመስጠትና በሀገሪቱ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በማድረግ ወንጀል የተጠረጠሩ አምስት ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ተጠርጣሪዎቹም የአዲስ አባባ የህወሓት ጽህፈት ቤት የቀድሞ ሃላፊ አቶ ተወልደ ገብረጻዲቅ፣ የህግና ፍትህ ዳይሬክተር አቶ ተስፋለም ይሕደጎ እና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የደህንነት ሃላፊ አቶ አጽብሃ አለማየሁ እና ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ናቸው።
መርማሪ ፖሊስ እስካሁን በተጠርጣሪዎች ላይ የሰራቸውን መርምራ ለፍርድ ቤቱ
ያብራራ ሲሆን፥ የሰው ምስክር መቀበሉንና የመንግስትን ሚስጥር አሳልፈው መስጠታቸውን የሚያስረዱ ማስረጃዎች መሰብሰቡን ተናግሯል።
በሀገሪቱ ሁከትና አመፅ እንዲፈጠር ሲሰሩ ነበር ያለው መርማሪ ፖሊስ፤ በሰኔ 22 እና 23 2012 ዓ.ም የሀገሪቱን ህገ መንግስት በሀይል ለማፍረስ ከሌሎች የሽብር ቡድኖች ጋር በመስራት ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስረድቷል። ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀን እንዲሰጠውም ጠይቋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው በድጋሚ ተይዘው መቅረባቸው ተገቢነት የለውም፤ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ አይገባም የሚል መቃወሚያ አቀርበዋል። ተጠርጣሪዎቹ በዋስ እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱ መዝገቡን አስቀርቦ መርምሮ ትዛዝ ለመስጠት ለነሃሴ 11 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።