Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ የብድር ክፍያ ሽግሽግ ስምምነት ተፈራረመች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ እፎይታ የሚሰጥ የብድር ክፍያ ሽግሽግ የመግባቢያ ስምምነት ከአበዳሪዎች ኮሚቴ ጋር ተፈራረመች፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር እንደገለጸው ስምምነቱ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የእዳ ሽግሽግ አማካኝነት የተፈረመ ሲሆን፥ ባለፈው መጋቢት ወር በመርህ ደረጃ የተደረሰውን የብድር ሽግሽግ በይፋ ተግባራዊ የሚያደርግ ነው።

ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ እፎይታ የሚሰጥና ለዓመታት ሲደረግ ለነበረው ድርድር ስኬታማ መቋጫ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ስምምነቱን አስመልክተው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት፥ በእስካሁኑ ሂደት የተንጸባረቀው የትብብር መንፈስ በሁለትዮሽ ስምምነቶች ሂደት ወቅትም እንደሚቀጥልና ሂደቱን ለማፋጠን እንደሚረዳ የጸና እምነት አለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከውጭ አበዳሪዎች ጋር በትብብር መስራቷን እንደምትቀጥል ገልጸው፥ ከሀገሪቱ የዕዳ ሽግሽግ ፍላጎትና ሁሉንም አበዳሪዎችን በተነጻጻሪ መንገድ ከማስተናገድ መርህ ጋር በሚጣጣም መልኩ ስምምነቶችን ለመፈፀም ትሰራለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከአበዳሪ ኮሚቴው ጋር የተደረሰውን መግባቢያ፣ የቦንድ ባለቤቶችን ጨምሮ ከሌሎች የውጭ አበዳሪዎች ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ የምታደርገውን ጥረት የበለጠ እንደሚያጠናክርም ነው የገለጹት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.