Fana: At a Speed of Life!

በትምህርት ዘርፍ የመረጃ ክፍተትን የሚቀርፍ የዲጂታል አሠራር…

አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በትምህርት ሥርዓት ውስጥ ለዓመታት ተግዳሮት ሆኖ የቆየውን የመረጃ ጥራት፣ ተዓማኒነትና አያያዝ ችግር ለመፍታት የሚያስችል አጠቃላይ የዲጂታል አሠራር በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት መረጃ አስተዳደርና አይሲቲ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰብስቤ ለማ ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት÷ የትምህርት ሥርዓቱን ለማዘመን የተለያዩ ርምጃዎች ተወስደዋል።

ከእነዚህም መካከል በወረቀት ላይ የተመሰረተውን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ወደ ዲጂታል መቀየር ዋነኛው እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም የመረጃ ክፍተቶችን በመሙላትና ለውሳኔ አሰጣጥ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በአዲሱ የዲጂታል ሥርዓት መረጃዎችን ከመሰብሰብ ጀምሮ በማጣራት፣ በመቆጣጠር እና ሪፖርት በማድረግ በትምህርት ዘርፍ ለሚወጡ እቅዶች፣ ፖሊሲዎች እንዲሁም ጥናትና ምርምሮች ግብዓት የሚሆን መረጃ እንደሚቀርብ አመልክተዋል።

በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በሀገር አቀፍ ደረጃ ባሉ ሁሉም የትምህርት ተቋማት ተግባራዊ መሆን የጀመረው ዲጂታል ሥርዓት÷ ተማሪዎችና መምህራን በሚሰጣቸው መለያ ቁጥር አጠቃላይ የትምህርት መረጃዎቻቸውን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ የዲጂታል ክህሎት ያለው የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎችን የማብቃት ሥራ መሰራቱንም አቶ ሰብስቤ አንስተዋል።

ይህ የዲጂታል ሽግግር ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ የጀመረችውን የሪፎርም ሥራ ከማገዙም በላይ የትምህርት ተቋማት ደረጃቸውን የጠበቀ የመረጃ አያያዝ ሥርዓቶችን እንዲከተሉ መንገድ ይከፍታልም ነው ያሉት።

በጸሎት መንገሻ

አቶ ሰብስቤ ለማ ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ሙሉ ቆይታ ማስፈንጠሪያውን በመጫን ይከታተሉ👇

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.