Fana: At a Speed of Life!

ከብሪክስ ጉባዔ ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ውይይቶች ተደርገዋል – ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከብሪክስ ጉባዔ ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር የጎንዮሽ ውይይቶችን በማድረግ ያለውን ትብብር የሚያጠናክሩ ውይይቶች ተደርገዋል አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በብራዚል የብሪክስ 17ኛ ጉባዔ ቆይታን በተመለከተ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከብሪክስ ጉባዔ ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር የጎንዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡

በውይይቶቹም ከሀገራቱ ጋር ያለውን የሁለትዮች ግንኙነትና ትብብር ለማጠናከር እንዲሁም ኢትዮጵያ በተለያዩ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ያላትን አቋምና ፍላጎት ተረድተው እንዲደግፉ ለማግባባት ጥሩ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከብራዝል ፕሬዚዳንት ሉላ ደ ሲልቫ ጋር የሀገራቱን ትብብር ለማጠናከር መምከራቸውን ጠቅሰው÷በተለይም የኢኮኖሚ ትብብርና ግንኙነትን ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ እና ቀጣናው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ፣ አቅጣጫ እና ፖሊሲ በአግባቡ እንዲረዱ ለማድረግ ጥሩ ዕድል መፈጠሩንም ነው ያስረዱት፡፡

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጋር ባደረጉት ውይይት÷ ኢትዮጵያና ቻይና ያላቸውን የተጠናከረ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን አብራርተዋል፡፡

በተለይም ቻይና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ያላትን አዎንታዊ አስተዋጽኦ የምታጠናክርበትንና በፓሪስ ክለብ ማዕቀፍ ቻይና የእዳ ሽግሽግ ለኢትዮጵያ እንዲደረግ የተጫወተችው ከፍተኛ ሚና በሚጠናክርበት አግባብ ላይ ተወያይተዋል፡፡

እንዲሁም ቻይና በቅርቡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ያመቻቸችውን ከቀረጥ ነጻ ኤክስፖርት ወደ ቻይና ማስገባት የሚችሉበትን መንገድ በተመለከተ የሃሳብ ልውውጥ አድርገዋል ነው ያሉት፡፡

ሊ ኪያንግ በበኩላቸው÷ ወደ ቻይና የሚላከው የኢትዮጵያ ቡና ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ማንሳታቸውን ጌዲዮን (ዶ/ር) አስታውሰዋል።

ከዚህ ባለፈም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አስረድተዋል፡

ሲሪል ራማፎሳ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር በነበሩበት ወቅት ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተገናኘ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን አንስተው÷ አሁን ግድቡ የደረሰበትን ደረጃ፣ የግድቡን መጠናቀቅ በተመለከተ እና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከእነዚህ ሀገራት ልምድ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢንቨስትመንት ማግኘት እንደምትፈልግ እና የምታበረክትባቸው የተለያዩ መስኮች መኖራቸውንም ጌዲዮን (ዶ/ር) ጠቅሰዋል፡፡

የብሪክስ ትብብር ሦስት የትኩረት አቅጣጫዎች እንዳሉት የጠቀሱት ሚኒስትሩ÷ የፖለቲካ እና ጸጥታ፣ የኢኮኖሚ እንዲሁም የባሕል እና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንደሚገኙበት አስገንዝበዋል፡፡

በተለይም በኢኮኖሚው መስክ ኢትዮጵያ ከእነዚህ ሀገራት ጋር ያላት ትስስር ለቀጣይ ዕድገት መሰረታዊ ስለሆነ ማጠናከር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Documentary YouTube www.youtube.com/@fanamcdocumentary በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.