Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዛሬው እለት በባህርዳር ከተማ በይፋ ተጀምሯል፡፡
የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምስክር ሰውነት ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፥ ክልል አቀፍ የክረምት የዜጎች በጎ አድራጎት የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በባሕርዳር ከተማ ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል የችግኝ ተከላ እና የፅዳት ዘመቻ የተከናወነ ሲሆን፥ በጎ ፈቃደኛ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለአረጋውያን ቤት ገንብቶ ለማስረከብ ቃል ገብተዋል፡፡
በቢሮው የወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ዘርፍ ኃላፊ አወቀ መንግስቴ በበኩላቸው÷ በዘንድሮው በክረምት የየበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ8 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን በ17 የስምሪት መስኮች ተሳታፊ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም 13 ነጥብ 8 ሚሊየን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ እንደሚሆን ገልጸው፥ የበጎ ፈቃድ አገልገሎቱ የክልሉ መንግስት ሊያወጣው የሚችለውን ከ7 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያድን አስረድተዋል፡፡

በአገልገሎቱ ትግበራ ሂደት በክልሉ ትኩረት የሚሹና የርብርብ ማዕከል ሊሆኑ ይገባል የተባሉ 14 የበጎ ፈቃድ ስራዎች መለየታቸውንና ሌሎች ተጨማሪ ሦስት የስምሪት መስኮች መለየታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ የቤት ግንባታ እና ጥገና አገልገሎቶች፣ የደም ልገሳ፣ የማዕድ ማጋራት፣ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርቶችና ነፃ የህክምና አገልግሎት ትኩረት የተሰጣቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፎች መሆናቸውን ነው ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡

የኮደርስ ስልጠና፣ የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማት እንዲሁም የትውልድ ግንባታ ሌሎች ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ከ65 በመቶ በላይ የሚሆነው የህብረተሰብ ከፍል ወጣት መሆኑን የጠቁሙት ሃላፊው÷ እነዚህ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አግልገሎቱ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.