Fana: At a Speed of Life!

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀዋሳ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ አኖሩ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል ውስጥ የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀዋሳ ከተማ ታቦር ተራራ ላይ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

የክልሉ መንግስት ከኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ጋር በመተባበር “በመንገድ ደህንነት ጉዳይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ይመለከታቸዋል” በሚል መሪ ሀሳብ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እና የእግር ጉዞ አካሂደዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መኩርያ ማርሻዬ በወቅቱ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ሰፊ ለዉጥ እያስመዘገበችበት ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታት 18 ሚሊየን ችግኝ በከተማ ደረጃ ተተክሎ 92 በመቶ ያህሉ መፅደቁን ገልጸው፤ የከተማን ዕድገት እና ንጽህና በጋራ ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።

ዘንድሮ በከተማዋ 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ መምህሩ ሙኬ በበኩላቸው፤ እስካሁን ድረስ በክልል ደረጃ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ችግኝ ተተክሎ 86 በመቶው እንደጸደቀ ገልጸዋል።

ክልሉ ዘንድሮ 307 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።

በሌላ በኩል በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚጠፋውን የሰዉ ሕይወት በጋራ እንታደግ በሚል መሪ ቃል የእግር ጉዞ ተካሂዷል።

በታመነ አረጋ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.