የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የህብረተሰቡን የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ እያሳደገ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን “የጽዱ ኢትዮጵያ” ንቅናቄ ህብረተሰቡ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያለውን ግንዛቤ እያሳደገ ነው አለ፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል “ጽዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድርግ” በሚል መሪ ሀሳብ 2ኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ማስጀመሪያ ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ (ኢ/ር) እንዳሉት፥ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተከናወነ የሚገኘው የጽዱ ኢትዮጵያ መርሐ ግብር ለነዋሪዎች ጤናማና ንፁህ አካባቢ ለመፍጠር የሚያግዝ ነው።
ንቅናቄው የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን በማዘመን ውብና ንፁህ አካባቢ እንዲፈጠር የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰው፥ የህብረተሰቡን የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ እያሳደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በመንግስት እየተከናወኑ የሚገኙት የወንዝ ዳርቻና የኮሪደር ልማት ስራዎች የጽዱ ኢትዮጵያ አካል መሆናቸውን የገለጹጽ ዋና ዳይሬክተሯ፥ አካባቢን ንፁህ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው፥ መርሐ ግብሩ ውጤታማ እንዲሆን በክልሉ የተጀመሩ የአረንጓዴ ቦታዎችን ልማት በማስፋፋትና ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን በመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመድረኩ ላይ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡