የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታው አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው አለ።
በሚኒስቴሩ የአየር ንብረት ለዉጥ ከፍተኛ ባለሙያ ይዘንጋው ይታይህ ለፋና ዲጅታል እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ በፈረንጆቹ 2015 የተደረሰውን የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ተቀብላ እየተገበረች ትገኛለች፡፡
ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢ ጥበቃ ተግባራትን እየከወነች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የካርበን ልቀትን ለመቀነስ ወሳኝ ርምጃዎችን እየወሰደች እንደሆነ ገልጸው÷ ከነዚህ ርምጃዎች መካከል በትራንስፖርት ዘርፍ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ስራ ማስገባት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በስፋት እንዲገቡ ሁኔታዎችን ማመቻችትን ጨምሮ በሀገር ውስጥ እንዲገጣጠሙ እንዲሁም የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን በመገንባት ረገድ ውጤት መምጣቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች የብዝሃ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት በተሰራው ስራ በርካታ የአሌክትሪክ አውቶብሶችን ወደ ስራ ገብተዋል ነው ያሉት።
በዚህም የአሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ መሆናቸውንም ነው አቶ ይዘንጋው የገለጹት፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ጤናማ ከባቢ አየር ከመፍጠር ባለፈ የነዳጅ ወጪ እንዲቀንስ በማድረግ ሚናቸውን እየተወጡ እንደሆነም አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ቀላል ባቡር እንዲሁም የጭነትና የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ያለውን የኢትዮ-ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ባቡር ለካርበን ልቀት ቅነሳ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ