ኢትዮጵያ እና ቻይና በዓለም አቀፍ መድረክ ትብብራቸው የበለጠ ውጤታማ ሆኗል – ፕሬዚዳንት ታዬ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ቻይና በዓለም አቀፍ መድረክ ትብብራቸው የበለጠ ውጤታማ እየሆነ መጥቷል አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ።
የ2025 የቻይና የህክምና በጎ ፈቃደኞች የአፍሪካ በጎ አድራጎት ተልዕኮና አለም አቀፍ የህክምና በጎ ፈቃደኞች ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተጀምሯል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የቻይና በጎ ፈቃደኞች ላሳዩት ቁርጠኝነት አመስግነው፥ በመርሐ ግብሩ በርካታ ልጆችና ተጨማሪ የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች አገልግሎቱን እንደሚያገኙ እምነታቸውን ገልጸዋል።
በጎ ፈቃደኞቹ በቆይታቸው ለእውቀት እና ክህሎት ሽግግር ትኩረት እንዲሰጡም ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ እና ቻይና በንግድ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረክም ትብብራቸው የበለጠ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል።
በመርሐ ግብሩ የልጆች የልብ ቀዶ ሕክምና፣ የዓይን ሞራ ግርዶሽ፣ የዐይን ህክምና፣ የማህፀን ቀዶ ሕክምናና ሌሎች የህክምና አገልግሎቶች ይሰጣሉ።
በተጨማሪም በአንድ የመንግስትና በአንድ የግል ትምህርት ቤት የዓይን እና የልብ ምርመራ የሚሰጥ ሲሆን፥ ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ሴቶች የማህፀን በር ካንሰር ምርመራ ይደረጋል፡፡