ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራን አስጀመሩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራን አስጀምረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ የኢትዮጵያን ፈጣን የአየር ትራንስፖርት እድገትና እየሰፋ የመጣውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ትስስር ዘላቂ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ወደ 25 ሚሊየን የሚጠጉ መንገደኞችን በዓመት የማስተናገድ አቅሙ ላይ ከደረሰው ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተጨማሪ አዲስ ሜጋ ጣቢያ እየለማ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ይህ የተለያዩ አውሮፕላን ማረፊያዎችን የመገንባት ስትራቴጂ ኢትዮጵያን የወደፊቷ የአፍሪካ ግምባር ቀደም የአየር ትራንስፖርት በር የማድረግ አላማን ያነገበ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት እንደሆነም አስገንዝበዋል።
አውሮፕላን ማረፊያው ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ የኢንዱስትሪ ማስፋፊያ አጀንዳ እና የረጅም ዘመን የአቪዬሽን ስትራቴጂ ጋር የተናበበና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንደሚያጠናክር ጠቅሰዋል።
በ”ኤኤፍሲኤፍቲኤ”ማዕቀፍ የአፍሪካን የማገናኘት አቅም እንደሚጨምር ጠቁመው ÷ የንግድ እና ቱሪዝም ኮሪደሮችን የሚያሰፋና ኢትዮጵያንም ቀዳሚ የበይነ አህጉር ማዕከል የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ደቡብ ምስራቅ 40 ኪሎ ሜትር አካባቢ የምትገኘውና 1 ሺህ 910 ሜትር ከፍታ ያላት ቢሾፍቱ ለአውሮፕላኖች ሥራ የተመቸ ከባቢ እንዳላት አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም መዳረሻቸውን ኢትዮጵያ ላደረጉም ሆነ ለትራንዚት መንገደኞች ብቁ ሁኔታ እንዳላት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ቢሾፍቱ ለአዲስ አበባ ያላት ቅርበት ከነባሩ የአየር ትራንስፖርት ምኅዳር ጋር በቀላሉ የተዋሃደ አሠራር እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ሲሉም አመልክተዋል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሥራ በዓመት 60 ሚሊየን ተጓዦችን የሚያስተናግድና ሲጠናቀቅም አፍሪካን ከዓለም ቀዳሚ የአየር ትራንስፖርት መነኸሪያዎች አንዷ እንደሚያደርጋት አንስተዋል፡፡
በዓመት 110 ሚሊየን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረውም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት፡፡