Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ለቅርስ ዕድሳት የሰጠው ትኩረት የቅርሶችን ደኅንነት መጠበቅ አስችሏል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት ለቅርስ ዕድሳትና እንክብካቤ የሰጠው ትኩረት የቅርሶችን ደኅንነት መጠበቅ አሰችሏል አለ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረ/ፕሮፌሰር) እንደገለጹት፥ መንግስት በቅርስ ጥበቃ ላይ የፈጠረው አዲስ ዕይታ ኢትዮጵያ ያላትን የካበተ የቅርስ ሃብት በመጠበቅ ወደ ሃብት መቀየር አስችሏል፡፡

በዚህም በርካታ የኢትዮጵያ የቅርስ ሃብቶች ላይ የዕድሳትና እንክብካቤ እንዲሁም የጥገናና የልማት ስራ እንዲከናወን ማስቻሉን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተከናወኑና በመከናወን ላይ የሚገኙ የቅርስ ዕድሳትና እንክብካቤ ስራዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር በተሞክሮነት የሚቀርቡ ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያውያንን ገናና ታሪክ በማስተዋወቅና ትውልድን በማነጽ ትልቅ ድርሻ ያለው የቅርስ ሃብትም በሀገር የቱሪዝም ገቢ ላይ ጉልህ ሚና እንዳለው ነው ዳይሬክተሩ ያስረዱት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለቅርስ ልማት የሰጡት ትኩረት ለቅርሶች ደኅንነትና ልማት አዲስ ምዕራፍ ከፍቷልም ነው ያሉት፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተከናወኑና እየተከናወኑ የሚገኙ የቅርስ ዕድሳትና ልማት ስራዎች የኢትዮጵያን ቅርሶች ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡

ብሔራዊ ቤተ መንግስት፣ አንድነት ፓርክ፣ የጎንደር አብያተ መንግስታትና የጅማ አባ ጅፋር ቤተ መንግስት የቅርሶችን ታሪካዊነትና የሀገርን ከፍታ በሚመጥን መታደሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን በአሁኑ ወቅት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን፣ የአክሱም ሐውልቶችን፣ የብሔራዊና የደሴ ሙዚየሞችን ጨምሮ ሌሎች ቅርሶችን የመጠበቅ፣ የመንከባከብና የማደስ ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

እድሳት የሚደረግላቸው የቅርስ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ ውስጥ በተሻለ ጥራት እንዲጠናቀቁ ትኩረት ተደርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.