ጳጉሜን 1 ሀገራችንን ወደ ብልፅግና ለማድረስ የጽናት መንፈሳችንን የምናድስበት ይሆናል – አይሻ መሀመድ (ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጳጉሜን 1 ኢትዮጵያውያን በቁርጠኝነት እና አንድነት ሀገራችንን ወደ ላቀ የብልፅግና ከፍታ ለማድረስ የጽናት መንፈሳችንን የምናድስበት ዕለት ይሆናል አሉ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር)፡፡
ጳጉሜን 1 የጽናት ቀንን ለማክበር የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
ዕለቱን በማስመልከት ሚኒስትሯ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዘመናት ህልማችንን ዕውን ባደረግንበት፣ በራዕይ፣ በማይታክት ጥረትና በአንድነት የተወለደው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድባችን ምረቃ ዋዜማ ላይ የጽናት ቀን መሆኑ ደስታችንን አጥፍ ድርብ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ግድቡ የሀገር ኩራት ምልክት፣ የህዝቡ የጽናት ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ የብልፅግና ጉዞ ለማሻገር ያለው አቅም የላቀ በመሆኑ ኩራት ይሰማናል ነው ያሉት።
የጽናት ቀንን ለማክበር ልዩ ልዩ የጥበብ ስራዎች፣ የጽናት ሸማኔዎቹ የተሰኘ ዶክመንተሪ ፊልም፣ ዲጅታል አውደ ርዕይ እንዲሁም ሌሎች በርካታ መርሐ ግብሮች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ጽናት የህዝቦቿ ጽናት ነውና የማያቋርጥ የስኬትና የድል መሰረት የሆነው ህዝባችንን የምናወድስበት፣ በፀጥታና ደህንነት መስኮች ላስመዘገብናቸው ሁለንተናዊ ስኬቶች ዋጋ የምንሰጥበት፣ ለወደፊቱም በጽናት መቆማችንን የምናውጅበት ነው ብለዋል፡፡
ነገ ከቀኑ 5 ሰዓት ከ30 ሲል ሁሉም በያለበት በመቆም የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር እየተዘመረ ሰንደቅ አላማ የሚሰቀል መሆኑን አመልክተዋል።
የጸጥታና ደህንነት አመራሮች እንዲሁም ሰራተኞች ባሉበት ሆነው የገቡትን ቃል ዳግም የሚያድሱበትና ቃለ መሃላ የሚያደርጉበት መርሃ ግብር ተዘጋጅቷል።
በዘመን በየነ