Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በመተማመን፣ በእውቀት እና መከባበር ላይ የተመሰረተ አጋርነት ለማሳደግ ቁርጠኛ ናት – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በመተማመን፣ በእውቀት እና በጋራ መከባበር ላይ የተመሰረተ አጋርነት ለማሳደግ ቁርጠኛ ናት አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሩሲያ እየተካሄደ በሚገኘው በዓለም የአቶሚክ ፎረም ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ኢትዮጵያ በኒውክለር ቴክኖሎጂ ከሩሲያ ጋር ያላትን አጋርነት በማጠናከር የአፍሪካ ተምሳሌት ለመሆን ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት እያደጉ ከሚገኙ ሀገራት መካከል እንደምትገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በርካታ የልማት እቅዶች እንዳሏትና አስተማማኝ፣ ንፁህ እና ቀጣይነት ያለው የኃይል አቅርቦትን የሚጠይቁ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የውሃ፣ ፀሐይ እና ንፋስ ኃይል ብቻ እየተጠቀመች ለወደፊት ያሰብነውን ያህል ማደግ አንችልም ሲሉም አጽንዖት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ከአስር ዓመታት በላይ መሪ እንደሆነችና በአፍሪካ ትልቁ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቁርጠኛነታችን ምልክት መሆኑን ያሳየንበት እንደሆነም አስረድተዋል።

የኒውክለር ቴክኖሎጂ አስተማማኝ ኃይል ለመፍጠር እና ለጠንካራ ደህንነት እንዲሁም የውሃ አጠቃቀምን ምቹ ለማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተው÷ ለኢትዮጵያ ኒውክለር የኃይል ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነም ተናግረዋል።

የኒውክለር ኃይልን በጥንቃቄ በማቀድና ጥቅም ላይ በማዋል ጠንካራ የሀገር ውስጥ አቅምን በመፍጠር ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀም መታቀዱን ጠቁመዋል።

የኒውክለር ሃይል በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ በኢንዱስትሪ እና በቴክኖሎጂ ፈጠራ ጠንካራ ተሳትፎ ለማድረግ ያግዘናልም ነው ያሉት፡፡

የሩሲያን የዘርፉን ተመራማሪዎች ከኢትዮጵያ የተማረ ሰው ሃይል ጋር በማጣመር ምሳሌ የሚሆን ትብብር በመፍጠር ለሕዝብ የሚጠቅምና ለአፍሪካ ተምሳሌት የሆነ የኒውክለር ቴክኖሎጂ ለመገንባት መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም በመተማመንና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ትብብር በማድረግ እና ተግዳሮቶችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ የጋራ ህልማችንን ወደ ውጤት መቀየር እንችላለን ብለዋል።

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.