Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ታዬ የፀጥታው ምክር ቤትን ለማሻሻል አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድና ለአፍሪካ ውክልና ቅድሚያ እንዲሰጥ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤትን ለማሻሻል አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ እና በማሻሻያው ለአፍሪካ ውክልና ቅድሚያ እንዲሰጥ  ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ በ80ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ለአፍሪካ የረጅም ጊዜ የፍትሕ መሻት ጥያቄ አቋራጭ ወይም ግማሽ መፍትሔ የለም ብለዋል።

በዕዳ ስረዛ ዙሪያ ባነሱት ሀሳብ አዲስ ዓለም አቀፍ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አመልክተው፤ በተለይ አፍሪካን ኢላማ ያደረጉ የኃይል እና የንግድ እቀባ እርምጃዎች በአፋጣኝ እንዲነሱ ጠይቀዋል።

በቀጣናችን ያለውን ዓለም አቀፍ ጸረ ሽብር ዘመቻ አጠናክረን እንቀጥላለን ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ በሶማሊያ ለተሰማራው የአፍሪካ ህብረት ድጋፍ ሰጭ እና አረጋጊ ኃይል ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ወደ ተግባር መግባቱን አስታውሰው፤ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ወደ መቋቋም ደረጃ  መቃረቡን ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ መመረቁ ኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ላልሆኑ 60 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን  ንጹህ የኃይል ምንጭ እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ግድቡ ለክልላዊ ትስስር ተስፋ የሚፈጥር እንደሆነ እና  በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኘው ከፍተኛ ድጋፍ እና ትብብር በናይል ተፋሰስ ሀገራት መካከል ትብብር ለመፍጠር የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሁለተኛ ትልቅ የሕዝብ ብዛት ያላት እና ከፍተኛ የባሕር ንግድ ያላት በቀይ ባህር እና በህንድ ውቅያኖስ የባሕር ላይ የባሕር ጉዞ ደኀንነት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥም ገልጸዋል።

በመልክዓምድራዊ ሁኔታዎች ምክንያት የትኛውም ሀገር የእድገት፣ የፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ እድሎች ዝግ መሆን እንደሌለበት ኢትዮጵያ እንደምታምን ተናግረዋል።

ከፍተኛ ባሕርን የሰው ልጅ የጋራ ቅርስ አድርጎ የሚገልጸው እና ሁሉንም ሀገራት በእኩልነት የመጠቀም መብትን የሚያረጋግጥ የዓለም አቀፍ ሕግ እውን መሆን አለበት ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እና በሕንድ ውቅያኖስ አካባቢ እኩል ልማት እና ደኀንነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ሁለንተናዊ አሰራር እንዲዘረጋ እንደምትሰራ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን ሕጋዊ  ፖሊሲዋን ለማሳካትም የዲፕሎማሲያዊ እና ሰላማዊ  አማራጮችን እንደምትከተል አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.