Fana: At a Speed of Life!

ዓለም ባንክ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም ባንክ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የባንኩ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጣና ም/ፕሬዚዳንት ንዲያሜ ዲዮፕ፡፡

ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ በ240 ሚሊየን ዶላር እየተከናወነ የሚገኘው የሞጆ አረንጓዴ ሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ ግንባታ በቅርቡ ይመረቃል፡፡

የዓለም ባንክ እና የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ከፍተኛ አመራሮችም የሞጆ አረንጓዴ ሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ ግንባታ የደረሰበትን ሁኔታ ተመልክተዋል፡፡

ንዲያሜ ዲዮፕ በዚህ ወቅት÷ የማስፋፊያ ግንባታው በተያዘው እቅድ መሰረት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ በመመልከታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ ዘርፍ መሳለጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ጠቅሰው÷ ይህም ሀገሪቱ በቀጣናው በዘርፉ ያላትን ተወዳዳሪነት ያሳድጋል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም መሰል ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ከማጠናከር ባለፈ ለሥራ እድል ፈጠራ ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው ነው ያሉት፡፡

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ማሪያም ሳሊም በበኩላቸው÷ ባንኩ በቀጣይ የኢትዮጵያን ሎጂስቲስ ዘርፍ ለማዘመን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በኢትዮጵያ በሎጂስቲክስ ዘርፍ የግል ሴክተሩን ለማሳተፍ የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው ÷ ለዘርፉ እድገት በትብብር መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የሞጆ አረንጓዴ ሎጂስቲክስ ማዕከል ማስፋፊያ ግንባታ አብዛኛው ሥራ በመጠናቀቁ በቅርቡ ለማስመረቅ ዝግጅት እየደረገ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ (ኢ/ር) ናቸው፡፡

የማስፋፊያ ግንባታ ሥራው የዓለም ባንክ ባስቀመጣቸው መስፈርቶች መሰረት መከናወኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.