በዓመት 111 ሚሊየን ሊትር የሚያመርተው የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ተመረቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሶማሌ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊየን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር መርቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ በሶማሌ ክልል ካሉብ በዓመት 111 ሚሊየን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር መርቀናል ብለዋል።
በተመሳሳይ በዓመት 1 ነጥብ 33 ቢሊየን ሊትር የማምረት አቅም የሚኖረውን ሁለተኛውን ዙር አስጀምረናል ነው ያሉት፡፡
ከፈሳሽ ተፈጥሮ ጋዝ ምርት ባሻገር በኃይል ማመንጫ ዘርፉም 1 ሺህ ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም በመያዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ፕሮጀክቱ የጋዝ ማምረቻ ብቻ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለማዳበሪያ ማምረቻ ወሳኝ የሆነውን ግብዓት በማቅረብ ለምግብ ሉዓላዊነት ጥረታችን የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
ለኃይል ማመንጫ እና የክሪፕቶ ማይኒንግ ሥራዎች አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን እንደሚያቀርብም አብራርተዋል።
ዛሬ በሶማሌ ክልል የተጀመሩት ከተያያዥ መሠረተ ልማቶች ግንባታ ጋር በአጠቃላይ ወደ 10 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች በተገቢ ክትትል እስከ መጠናቀቂያቸው ይደርሳሉ ነው ያሉት፡፡
የጀመርነውን ለመጨረስ ሁልጊዜም በጽናት እንደሠራነው ሁሉ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ይደርሳሉ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አጽንኦት ሰጥተዋል።