አባገዳ ጎበና ሆላ የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል መጠናቀቅን በማስመልከት ምስጋና አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ እሴቱን ጠብቆ መከበሩን አስመልክተው ምስጋና አቀረቡ።
አባገዳ ጎበና ሆላ ‘ኢሬቻ ለሀገር ማንሠራራት’ በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ በድምቀት የተከበረውን የ2018 ዓ.ም ሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ ኢሬቻ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ቋንቋና ባህል በድምቀት ያከበሩት በዓል ነው ብለዋል።
በዓሉ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ መከናወኑን ጠቅሰው፤ የአንድነት፣ የመተባበርና የሰላም መገለጫ በሆነው በዓል ላይ ከኢትዮጵያውያን አልፎ በርካታ የውጭ ዜጎች መሳተፋቸውንም ተናግረዋል፡፡
የሆረ ፊንፊኔ ኢትዮጵያውያን ወንድማማችና የጋራ እሴት ያለን መሆኑን ያሳየንበት ነው በማለት ገልጸው፤ በዓሉ የአንድነት፣ የጥንካሬና የመከባበር እሴት ማሳያ ሆኖ በድምቀት ተከብሯል ነው ያሉት።
በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባና ኦሮሚያ የጸጥታ ሀይሎች ሚናቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል ብለዋል።
ሌሎች ተቋማትም ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ስምሪት ማድረጋቸውን ገልጸው፤ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በአምስቱም የመግቢያ በሮች ለኢሬቻ ተሳታፊዎች ላደረጉት የሞቀ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአጠቃላይ በዓሉ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ላደረጉ የፌዴራል፣ የአዲስ አበባ ከተማ እና ኦሮሚያ ክልል መንግስት የከበረ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።