አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ መለያ ቁጥር ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አዲሱን የተሽከርካሪ ሰሌዳ መለያ ቁጥር ይፋ አድርጓል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ሚኒስቴሩ አዲስ የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሰሌዳ አይነቶችና ምልክቶች መወሰኛና የአገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 1050/2017 ማዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡
በመመሪያው መሰረትም የተሽከርካሪ ሰሌዳ መለያ ቁጥር በአዲስ እንደሚተካ ነው ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረው የተሽከርካሪ መለያ ቁጥር ሰሌዳ አመራረትና አሰረጫጨት የአሰራር ክፍተት እና የሃብት ብክነት ይስተዋልበት ነበር ብለዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ነባሩ የተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ ቁጥር በአዲስ መተካቱን ጠቁመው÷ አዲሱ ሰሌዳ ከዚህ ቀደም የነበሩ የአሰራር ችግሮችን እንዲቀርፍ የአሰራር ሥርዓት የተዘረጋለት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አዲሱ የሰሌዳ ቁጥር ኢትዮጵያን የሚገልጹ መለያዎችን የያዘ እንዲሁም ዓለም ዓቀፍ መስፈርቱን የተከተለ ሲሆን÷ 50 ሺህ ታርጋዎችም በማሳያነት ተዘጋጅተዋል፡፡
የዲጂታል ሥራው ተጠናቅቆ የቅየራ ሒደቱ በቅርቡ ወደስራ እንደሚገባ የተናገሩት ሚኒስትሩ÷ በ2018 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ቀይሮ ለመጨረስ ዝግጅት መደረጉን አጽንኦት ሰጥተዋል፡
በአሸናፊ ሽብሩ