Fana: At a Speed of Life!

በድሬዳዋ ከተማ የተገነቡ የተለያዩ ፋብሪካዎች ለአገልግሎት ክፍት ተደረጉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በድሬዳዋ ከተማ ግንባታቸው የተጠናቀቁ አዳዲስ ፋብሪካዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።

በዛሬው ዕለት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉት የብረት፣ የማዳበሪያ ከረጢት፣ የታሸገ ውሃ፣ የዱቄትና የፕላስቲክ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እና የከተማዋ ከንቲባ ከድር ጁሀርን ጨምሮ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በተሰሩ ስራዎች በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል።

ዛሬ የተመረቁት ፋብሪካዎችም ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት፣ የምርት ብክነትን በመቀነስና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ፋይዳቸው የላቀ መሆኑን አንስተዋል።

በ2017 የበጀት አመት ብቻ 4 ነጥብ 53 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን አስታውሰዋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፥ ከለውጡ ወዲህ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት ድሬዳዋን የኢንዱስትሪ ማዕከል እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።

በከተማ አስተዳደሩ በስራ ላይ የሚገኙ 69 ፋብሪካዎች ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሪ እያስገኙ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ለባለሃብቶች እየተደረገ የሚገኘው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በተስፋዬ ኃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.