የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሰራ ነው – ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጤና ሚኒስቴር የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆን እየተሰራ ነው አለ፡፡
በሚኒስቴሩ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ህይወት ሰለሞን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት፥ ክትባቱ አሁን ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ 58 ወረዳዎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡
እነዚህ ወረዳዎች የወባ በሽታ ስርጭቱ ከፍ ብሎ የሚታይባቸው መሆናቸውን ገልጸው፥ በቀጣይም በሁለተኛ ዙር ክትባቱ በሌሎች አካባቢዎች እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ክትባቱ በተለዩት 58 ወረዳዎች እድሜያቸው ከ5 አመት በታች የሆኑ ሁሉም ህፃናት የሚሰጥ ሲሆን፥ ይህን መሸፈን የሚያስችል ግብአት ወደ ወረዳዎቹ ገብቷል ነው ያሉት፡፡
የወባ በሽታ መከላከያ ክትባቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን መሪ ስራ አስፈዋሚዋ ጠቁመዋል።
የወባ በሽታ መከላከያ ክትባቱ መሰጠት በተጀመረባቸው አካባቢዎች ያሉ ዜጎች ልጆቻቸውን በማስከተብ ተባባሪ እንዲሆኑም አሳስበዋል።
በዙፋን ካሳሁን