በሰሜን ሸዋና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ ለመከላከል እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ መንጋ ለመከላከል እየተሰራ ነው አለ የግብርና ሚኒስቴር።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ ም/ሃላፊ ሃሰን ሰይድ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በብሔረሰብ አስተዳደሩ የተወሰኑ ወረዳዎች ላይ የግሪሳ ወፍ መንጋ ተከስቷል።
ዘንድሮ የተከሰተው የወፉ መንጋ ከተጠበቀው ጊዜ አስቀድሞ በመሆኑ በደረሰ የመኸር ሰብል ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ መሰረትም የአካባቢው አርሶ አደሮች የወፍ መንጋውን በባህላዊ መንገድ በወንጭፍና ድምፅ በማሰማት ለመከላከል ጥረት እያደረጉ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በብሔረሰብ አስተዳደሩ ጂሌ ጥሙጋና ደዋ ጨፋ ወረዳዎች ላይ የወፉ መንጋ በስፋት መታየቱን አመልክተዋል።
በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አበበ ጌታቸው ፥ የግሪሳ ወፍ መንጋ በተወሰኑ የዞኑ ወረዳዎች መከሰቱን ተናግረዋል።
መንጋው ጉዳት እንዳያስከትል በባህላዊ እና ዘመናዊ መንገድ ለመከላከል ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ ከበደ ላቀው በበኩላቸው ፥ በዞኖቹ የግሪሳ ወፍ መንጋ ክስተት መኖሩን በተመለከተ ለሚኒስቴሩ ሪፖርት መቅረቡን አረጋግጠዋል።
የሰብል ምርታማነት ላይ ተጽዕኖ የሚያስከትሉ ችግሮችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ዝግጁነት እንዳለ ገልጸው ፥ የግሪሳ ወፍ መንጋው ጉዳት እንዳያስከትል የሎጂስቲክ ማጓጓዝ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የኬሚካል ርጭቱ በአፋጣኝ የሚከናወን መሆኑንም አቶ ከበደ አመልክተዋል።
በሶስና አለማየሁ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!