በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ለአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቋል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ውብሸት ዘነበ እንዳሉት፥ በመርሐ ግብሩ በክልሉ 25 ሚሊየን የተለያዩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ይተከላሉ።
በዚህ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ላይ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ የክልሉ ሕዝብ እንደሚሳተፍ ገልጸው፥ 10 ሺህ በሚጠጋ ሄክታር መሬት ላይ የችግኝ ተከላው እንደሚከናወን ነው ያብራሩት።
885 የችግኝ ተከላ ቦታዎች መለየታቸውንና በቂ ችግኝ፣ ጉድጓድና ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ የሕዝቡ ባሕል እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፥ በነገው ዕለት በሚካሄደው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ ሕዝቡ ከማለዳ ጀምሮ በነቂስ ወጥቶ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።