አቶ አህመድ ሽዴ ከዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ግጭቶች መፍቻ ማዕከል ዋና ፀሐፊ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ግጭቶች መፍቻ ማዕከል ዋና ፀሐፊ ማርቲና ፖላሴክ ጋር ኢትዮጵያ የማዕከሉ አባል በምትሆንባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
አቶ አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት÷ መንግስት ለባለሃብቶች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ግጭቶች መፍቻ ማዕከልን (ICSID) ከተቀላቀለች ሀገሪቱን ከዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ማህበረሰብ ጋር ለማዋሃድ እንዲሁም የባለሃብቶችን አመኔታ ለማሳደግ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የማዕከሉ አባል መሆን የንግዱን ዘርፍ ለማሳለጥ፣ የግሉን ዘርፍ ለማጠናከር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡
የማዕከሉ ዋና ፀሐፊ ማርቲና ፖላሴክ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ማዕከሉን ለመቀላቀል ያላትን ፍላጎት በማድነቅ በአባልነት ሂደቱ የቴክኒክ ድጋፍ እና መመሪያ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያሳየችው ፍላጎትም በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት እና ለዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች ኢትዮጵያ የማዕከሉ አባል ለመሆን በምታደርገው ጥረት ተቀራርቦ ለመስራት እና በአዲስ አበባ የቴክኒክ አውደ ጥናት እንዲዘጋጅ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡