Fana: At a Speed of Life!

በአዋጁ የተከለከሉት የፕላስቲክ ከረጢቶች የትኞቹ ናቸው?

አዲስ አበባ፣ ጥር 29 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን መጠቀም የሚከለክለው አዋጅ ካሳለፍነው ጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

ሕብረተሰቡም አዋጁ የወጣበትን ዓላማ በመረዳት የተከለከሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን ባለመጠቀም የበኩሉን ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ በአዋጁ የተከለከሉ የፕላስቲክ ከረጢቶች የትኞቹ ናቸው የሚለው በሕብረተሰቡ ዘንድ ግርታ መፍጠሩን ፋና ዲጂታል ባደረገው ቅኝት ለመረዳት ችሏል፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው ባለሱቆች እና ሸማቾች እንደሚሉት÷ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶች የሚለው ሃሳብ በተወሰነ መልኩ ግርታን ፈጥሯል፡፡

ስለሆነም የፕላስቲክ ከረጢቶች ማለትም አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ እና መልሶ ዑደት (ሪሳይክል) የሚደረጉትን በተመለከተ ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የከተማ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ክትትል ዴስክ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ዓለሙ ለፋና ዲጂታል በሰጡት ማብራሪያ÷ በአዋጁ የተከለከሉት የፕላስቲክ ከረጢቶች በተለምዶ “ፌስታል” ተብለው የሚጠሩት ናቸው፡፡

እነዚህ ፕላስቲኮችም አንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ ውለው በቀጥታ የሚወገዱ ሲሆን÷ በመልሶ ዑደትም ጥቅም ላይ እንደማይውሉ አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሰረት ክልከላው ኩርቱ በሚል ስያሜ የሚታወቀውን ፌስታል ጨምሮ በተለያየ ዲዛይን የተሰሩና በቀላሉ በስብሰው ከአፈር ጋር የማይዋሃዱ የፕላስቲክ ከረጢቶች ወይም ፌስታሎችን እንደሚያካትት አብራርተዋል፡፡

ከጥር 23 ቀን ጀምሮ ባለው የትግበራ ሒደት ላይ ዳሰሳ መደረጉን ጠቁመው÷ በዚህም ሕብረተሰቡ አዋጁን ለመተግበር ያሳየው ተነሳሽነት የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

በአተገባበር ሒደቱ ላይ ከግንዛቤ ማነስ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለማስተካከል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡

ለዚህም መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻዎች በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመው÷ ሕብረተሰቡም የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል ከፕላስቲክ ያልተሰሩ የተኪ መያዣዎች ዋጋ ገበያ ላይ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸው÷ ይህም ሁሉም ባለድርሻዎች በቂ ዝግጅት ባለማድረጋቸው የተከሰተ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከፕላስቲክ ያልተሰሩ የተኪ መያዣዎችን አቅርቦት ለማሳደግ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ 1383/2017 መሰረት የፕላስቲክ ከረጢቶችን የተጠቀመ ወይም ለመጠቀም ይዞ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብ ከ2 ሺህ ብር የማያንስ ከ5 ሺህ ብር የማይበልጥ የገንዘብ ቅጣት ይጣልበታል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.