በመኸር ወቅት ከለማው ስንዴ 175 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል – አቶ አዲሱ አረጋ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2017/18 የምርት ዘመን የመኸር ወቅት ከለማው 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት የስንዴ ሰብል 175 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል አሉ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሀገር አቀፍ የስንዴ ልማት የመስክ ቀን የተካሄደ ሲሆን፤ በሚኒስትሩ የተመራ ቡድን በዞኑ ዶዶላ እና አዳባ ወረዳዎች የስንዴ ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
አቶ አዲሱ አረጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በዘንድሮ መኸር እንደ ሀገር በተለያዩ ሰብሎች ከተሸፈነው 20 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት 653 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።
ከዚህም ውስጥ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል የተሸፈነ መሆኑን ጠቅሰው፥ 2 ነጥብ 9 ሚሊየን ሄክታር ያህሉ በኩታገጠም የለማ እንደሆነ አመልክተዋል።
በስንዴ ከተሸፈነው መሬት 175 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸው፥ ይህም በስንዴ ራሳችንን ለመቻል የጀመርነው ስራ በየዓመቱ እድገት እየተመዘገበበት እንደሆነ ያሳያል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካይ ከ700 ሚሊየን እስከ 1 ቢሊየን ዶላር በማውጣት የስንዴ ምርት ከውጭ ስታስገባ እንደነበር አስታውሰው፥ ባለፉት ዓመታት ስንዴ በጋ ከክረም በስፋት በማልማት የውጭ ምንዛሬ ወጪውን ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።
ይህም ሀገራችን ያላትን ዕምቅ የተፈጥሮ ጸጋ እና የሰው ኃይል መጠቀም ከቻለች የምግብ ሉዓላዊነቷን ከማስጠበቅ አልፋ ሌሎችን መመገብ የምትችልበት አቅም እንዳላት አመላካች ነው ብለዋል።
በኃይለማርያም ተገኝ