Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ከውጭ ቱሪስቶች እንቅስቃሴ 155 ቢሊየን ብር ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት በመዲናዋ ከተደረጉ የውጭ ቱሪስቶች እንቅስቃሴ 155 ቢሊየን ብር ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ ተደርጓል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

ከንቲባዋ በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የቱሪዝም እንቅስቃሴን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት ነው ይህንን ያሉት፡፡

በዚህም የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለከተማዋ ዕድገት ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ለማሳደግ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲለሙ መደረጉን አመልክተዋል፡፡

ወደ ከተማዋ የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ እንደሚገኝ ጠቁመው÷ ባላፉት ስድስት ወራት 4 ነጥብ 9 ሚሊየን የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች በመዲናዋ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ባለፉት ስድስት ወራት 699 ሺህ 761 የውጭ ሀገር ቱሪስቶች አዲስ አበባን መጎብኘታቸውን ገልጸው÷ ከዚህም 155 ቢሊየን ብር ወደ ኢኮኖሚ ፈሰስ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በመዲናዋ ሲከበሩ የነበሩ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት እንዲሁም የስፖርትና የጤና ቱሪዝም በቱሪዝም እድገቱ ላይ ከፍተኛ አበርክቶ እንደነበራቸው አብራርተዋል፡፡

አዲስ አበባን የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተከናወኑ በርካታ የልማት ስራዎችና ሜጋ ፕሮጀክቶች በከተማዋ ውስጥ የሚደረጉ ኩነቶች እንዲጨምሩ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 150 የሚሆኑ ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ ኩነቶች አዲስ አበባ ላይ መካሄዳቸውን የጠቆሙት ከንቲባዋ÷ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻፀር 50 በመቶ ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.