በኦሮሚያ ክልል የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማልማት በትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን፡፡
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በክልሉ የሚገኙ እምቅ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ይበልጥ በማልማት ዘርፉን ለማጠናከር ትኩረት ተደርጓል፡፡
በዚህ መሰረትም የቱሪስት መዳረሻ መሰረተ ልማቶችን ከማልመት ጀምሮ የማስተዋወቅ ሥራዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ባሌ ብሄራዊ ፓርክን ጨምሮ ሌሎች በክልሉ የተሰሩ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎች ዘርፉን ከማጠናከር አንጻር ጉልህ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡
የባሌ ብሄራዊ ፓርክ የአካባቢውን ሁለንተናዊ እድገት በማፋጠን ታሪክ ቀያሪ መሆኑን ጠቁመው÷ለሀገር ኢኮኖሚ እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል፡፡
ክልሉን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት አቶ ነጋ÷ በ2017 በጀት ዓመት በርካታ የሀገር ውስጥና ከ200 ሺህ በላይ የውጭ ጎብኚዎች የክልሉን የቱሪስት መዳረሻዎች ተመልክተዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት የቱሪዝም አገልግሎት ጥራትንና መሰረተ ልማትን እንዲሁም የቱሪስት ቁጥርን ለመጨመርና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ የኮንፈረንስ ቱሪዝም በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መሆኑን አንስተው ÷ ለአብነትነም በጅማ፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱ እና ባቱ ከተሞች በዘርፉ ከፍተኛ እንቅስቃሴ መኖሩን ተናግረዋል፡፡
የክልሉን የቱሪስት መዳረሻዎች ይበልጥ ከማስተዋወቅ ረገድም መገናኛ ብዙሃን፣ የግሉ ዘርፍ እና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸው ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአቤል ነዋይ