በመዲናዋ የኮሪደር ልማቱን የሚመጥን የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በከተማዋ የኮሪደር ልማቱን የሚመጥን የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታና ጥገና ሥራ እየተከናወነ ነው አለ።
የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢያሱ ሰሎሞን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ፤ በመዲናዋ የሚገኙ የተለያዩ መንገዶች የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ አስፈላጊው ግንባታና ጥገና እየተደረገ ነው።
በዚህም በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በአጠቃላይ 328 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ሥራ ለማከናወን ታቅዶ ከ393 ኪሎ ሜትር በላይ ለሚሆን መንገድ ጥገና መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህ መሰረትም ከ14 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆን የአስፓልት መንገድ ጥገና ሥራ መከናወኑን አመልክተዋል።
በተመሳሳይ የኮብልስቶን እና የጠጠር መንገድ ግንባታ እና ጥገና ሥራ መከናወኑን ነው ሃላፊው ያስረዱት፡፡
የመንገድ ብልሽት መንስኤዎች መካከል የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ችግር አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከ104 ኪሎ ሜትር በላይ ለሚሆኑ መንገዶች የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ጥገና መከናወኑን ጠቁመዋል።
በጥገና ወቅት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ተገቢው ጥንቃቄ እንደሚደረግ ገልጸው፤ የሰዎች እንቅስቃሴ በሚቀንሱባቸው የእረፍት ቀናት እና ምሽት ላይ የጥገና ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ከ20 ዓመት በላይ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ መንገዶች የማሻሻያ ዲዛይን ተሰርቶላቸው በአዲስ መልክ ተሻሽለው እየተገነቡ ሲሆን÷የኮሪደር ልማቱን የሚመጥን የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ እየተከናወነ ነው፡፡
እንዲሁም በ2018 በጀት ዓመት ሁሉንም የመንገድ ጥገና ሥራዎች አካትቶ 854 ነጥብ 97 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመንገድ ጥገና ሥራ ለማከናወን መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡
በሶስና አለማየሁ