እሁድን ለበጎ ፈቃድ ስራ የሚያውሉት ጋሽ ፍሬው…
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እሁድን ለእረፍት ሳይሆን ለአካባቢ ጥበቃ በጎ ፈቃድ ስራ ማዋል ከጀመሩ ሰነባብተዋል ጋሽ ፍሬው ከፍያለው።
በአካባቢ ጥበቃ የበጎ ፈቃድ ስራ ላይ የተሰማሩት ፍሬው ከፍያለው የሥነ ልቦና ባለሙያና የተለያዩ ድርጅቶችን የማማከር ስራ ይሰራሉ።
ጋሽ ፍሬው ከፍያለው ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት÷ አካባቢ ጥበቃን ከግለሰብ ጤና ጋር በማዋሃድ በሀገሪቱ ውስጥ ዘላቂ የሆነ የአካባቢ ጥበቃ ተሳትፎ እንዲስፍን የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ነው።
ብዙዎች የሚያውቋቸው በጋሽ ፍሬው በሚል መጠሪያ ሲሆን÷ እሳቸውም በዚህ ደስ እንደምላቸው ተናግረዋል።
እሁድን ለእረፍት ሳይሆን ለአካባቢ ጥበቃ በጎ ፈቃድ ስራ ማዋል ከጀመሩ የሰነበቱ ሲሆን÷ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግን ከቆሻሻ መልቀም ጋር በማጣመር “ፕሎጊንግ (Plogging) ኢትዮጵያ” የሚል እንቅስቃሴን ያስጀመሩ እና መስራችም ናቸው፡፡
ቆሻሻው የሌላ ሰው ቢሆንም ምድሯ ግን የኔ ናት” የሚሉት ጋሽ ፍሬው÷ በአንጦጦ አካባቢ በሳምንት አንድ ጊዜ በእግር በሚጓዙበት ወቅት ቆሻሻ እየለቀሙ በመሄድ የጀመሩት ልማድ ከራሳቸው አልፎ ቤተሰባቸው ብሎም ሌሎች በጎ ፈቃደኞች እንዲነሳሱ አድርጓል፡፡
እንጦጦ ተገኝተው በሚያደርጉት የፅዳት እንቅስቃሴ ከራሳቸው ጋር የሚነጋገሩበትና እውነተኛ ሳቅ ከሌሎች ጋር የሚጋሩበት ከመሆኑም በላይ ከፍ ለማለት ዝቅ ማለት እንደሚያስፈልግ የምለማመድበትም ነው ሲሉም ይገልጻሉ፡፡
በዚሁ ተግባር ላይ እያሉ በአጋጣሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አግኝቷቸው ደስ ከሚል የፊት ገፅታቸው ባሻገር በርቱ የሚል ግብረ መልስ እንደሰጧቸው ጠቅሰዋል፡፡
ከጊዜ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለሳቸው ያነሱት ሐሳብ ተጨማሪ ኃላፊነትና ብርታት እንደሆናቸውም ተናግረዋል፡፡
የደረስኩበት ሁሉ ሀገሬ ነው የሚሉት ጋሽ ፍሬው÷ በሙያቸው የተለያዩ ሀገራትን ተጉዘው አገልግለዋል፤ ተምረዋልም። ከእነዚህም ሀገራት ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ እንዲሁም አሜሪካ ይጠቀሳሉ፡፡
በቅድስት ዘውዱ
ጋሽ ፍሬው ከፍያለው ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ👇
https://www.youtube.com/watch?v=CoYkqseoVZM