የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ የግሉ ዘርፍ ድርሻ ሊጠናከር ይገባል
አባይ ሆምስ ሪል ስቴት የዳውንታውን ፕሮጀክቱን በሜክሲኮ አፍሪካ ህብረት ጎረቤት በይፋ አስመርቋል፡፡
የአባይ ሆምስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ምንተስኖት ታደሰ እንዳሉት÷በአዲስ አበባ የሚስተዋለውን የቤት አቅርቦች ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በትብብርና በትኩረት መስራት ይገባል፡፡
ከመንግስት ባሻገር በግሉ ዘርፍ እና በማህበራት በመደራጀት የሚከናወኑ የቤት ልማት ሥራዎችን መደገፍ እና ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አባይ ሆምስ በሜክሲኮ ጠማማ ፎቅ ፊት ለፊት በሚገኘው ይዞታው ላይ 3B+G+30 የሆነ ግዙፍ እና በርካታ አገልግሎቶችን የያዘ ቅይጥ የንግድና የመኖሪያ ህንጻ ለመገንባት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ ገብቷል።
ፕሮጀክት 12 ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታ ውስጥ ያረፈ ሲሆን ÷ ምቹ በቂ የሆነ የመኪና ማቆሚያ፣ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ቻርጅ ማድረጊያ፣ የከርሰ ምድር ውሃ፣ለህጻናት እና አዋቂዎች የሚሆኑ 2 የዋና ገንዳዎችን ይዟል፡፡
በተጨማሪም የጋራ መዝናኛ ስፍራን፣ ለእያንዳንዱ ህንጻ 8 አሳንሰሮችን እንዲሁም ሌሎች በርካታ መገልገያዎችን በውስጡ ያካተተ ምቹ የንግድ ማእከል እና የመኖሪያ ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አባይ ሆምስ የግንባታ ጥራት ጉድለትን ለመቅረፍና ለመኖርም ሆነ ለስራ የሚመች ዘመናዊ ዲዛይን፣ ለኢንቨስትመንት አዋጭ በሆነው ሜክሲኮ አፍሪካ ህብረት ጎረቤት ይዞ መቅረቡንም አመልክተዋል፡፡