Fana: At a Speed of Life!

ምርጥ ብቃት ላይ የሚገኙ የፊት መስመር ተጫዋቾች …

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለቡድናቸው እና ለሀገራቸው ግቦችን በማስቆጠር ጥሩ ጊዜ እያሳለፉ የሚገኙ ምርጥ የፊት መስመር ተጫዋቾች ናቸው፡፡
ኖርዌያዊው ኤርሊንግ ብራውት ሃላንድ፣ እንግሊዛዊው ሃሪ ኬን እና ፈረንሳዊው ኪሊያን ምባፔ፡፡
የ25 ዓመቱ የማንቼስተር ሲቲ የፊት መስመር ተጫዋች ሃላንድ በ2025/26 የውድድር ዓመት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ባደረጋቸው 11 ጨዋታዎች 14 ኳሶችን ከመረብ ጋር በማገናኘት የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ደረጃን ይዟል፡፡
በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ደግሞ ለሲቲ ባደረጋቸው 4 ጨዋታዎች ልክ እንደ ወቅቱ ምርጦች ሃሪ ኬን እና ኪሊያን ምባፔ 5 ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡
ለሀገሩ ኖርዌይ ደግሞ በዚህ የውድድር ዓመት እስካሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች 14 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
ፈረንሳዊው የፊት መስመር ተጫዋች ኪሊያን ምባፔ ሌላው በዚህ የውድድር ዘመን ድንቅ ጊዜ እያሳለፉ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡
የሪያል ማድሪዱ ተጫዋች ኪሊያን ምባፔ በስፔን ላሊጋ በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው 12 ጨዋታዎች 13 ግብ በማስቆጠር የላሊጋውን ከፍተኛ ግቢ አግቢዎች ደረጃ በመምራት ላይ ይገኛል፡፡
በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ቡድኑ ድል እንዲያደርግ ትልቁን አስተዋፅኦ እያበረከተ የሚገኘው ኪሊያን ምባፔ በ4 ጨዋታ 5 ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
የ26 ዓመቱ ኪሊያን ምባፔ ለሀገሩ ፈረንሳይ በ2025/26 እስካሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች 5 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
እንግሊዛዊው የ32 ዓመቱ የባየርን ሙኒክ የፊት መስመር ተጫዋች ሃሪ ኬን በዚህ የውድድር ዓመት ስኬታማ ጊዜ እያሳለፈ ሲሆን፤ በውድድር ዓመቱ በጀርመን ቡንደስሊጋ እስካሁን ባደረጋቸው 10 ጨዋታዎች 13 ግብ በማስቆጠር የቡንደስሊጋውን ኮከብ ጎል አስቆጣሪነት እየመራ ነው፡፡
በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ለሙኒክ ባደረጋቸው 4 ጨዋታዎች 5 ግብ በማስቆጠር ድንቅ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል፡፡
በዲኤፍቢ ፖካል 4 እና በሱፐር ካፕ ደግሞ 1 ግብ ማስቆጠር የቻለው ሃሪ ኬን በሁሉም ውድድር ለሙኒክ 3 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡
ሃሪ ኬን ለሀገሩ እንግሊዝም 6 ግቦችን በማስቆጠር በብሔራዊ ቡድኑ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል፡፡
ምርጥ ብቃታቸውን እያሳዩ የሚገኙት ሦስቱም ተጫዋቾች በሚጫወቱበት ሊግ የኮከብ ግብ አስቆጣሪነት ደረጃውን እየመሩ ይገኛል፡፡
የወቅቱ የፊት መስመር ድንቅ ተጫዋቾች በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ በተመሳሳይ 5 ግቦችን ያስቆጠሩ ሲሆን ማን የተሻለ ሆኖ የውድድር ዓመቱን ያጠናቅቃል የሚለው ይጠበቃል፡፡
በወንድማገኝ ፀጋዬ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.