Fana: At a Speed of Life!

የኢጋድ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በትኩረት የሰሩ ጋዜጠኞች ሽልማት ሥነ ሥርዓት በኢትዮጵያ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ)   ኢትዮጵያ 3ኛውን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በትኩረት የሰሩ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሽልማት ሥነ ሥርዓት ታስተናግዳለች፡፡

ኢጋድና የኢትዮጵያ መንግስት በጋር የሚያዘጋጁት የሽልማት መርሐ ግብሩ÷ በፈረንጆቹ 2025 ከሕዳር 29 እስከ 30 ቀን በስካይ ላይት ሆቴል ይካሄዳል፡፡

ሽልማቱ የቀጣናው መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ከባቢን ለመፍጠር ውጤታማ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ታሪኮችን እንዲያዘጋጁ ያበረታታል፡፡

ባለሙያዎቹ የእርስ በርስ ትስስራቸውን በማጠናከር የሚሰሯቸው ዘገባዎች በአካባቢው ሀገራት ተደራሽ ለማድረግ ሚናው ጉልህ መሆኑንም የኢጋድ መረጃ ያመላክታል፡፡

ከመርሐ ግብሩ ጎን ለጎን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የልምድና እውቀት ሽግግር፣ የፈጠራ ልውውጥ፣ የአቻ ትምህርት እንዲሁም በጋዜጠኞች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች እና የልማት አጋሮች መካከል ምክክር ይካሄዳል፡፡

ተሸላሚዎችን የመለየቱ ሒደት ከኢጋድ አባል ሀገራት በተወጣጡ የዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች የጋዜጠኝነትን መርሆችን መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ 3ኛውን የኢጋድ የጋዜጠኞች ሽልማት ማዘጋጀቷ በቀጣናዊ ትብብር፣ በአየር ንብረት ለውጥ ዲፕሎማሲ እና በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ልማት ያላትን ሚና ለማጠናከር ያስችላል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.