ዜጎችን በተመጣጣኝ ድጋፍ የቤት ባለቤት የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤት ልማት መርሐ ግብር በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የከተማ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ድጋፍ የቤት ባለቤት ለማድረግ እየተሰራ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሉት÷ ከተሞች የተቀየሰውን የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ትልቅ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የብልጽግና ጉዞውን አጠናክሮ በማስቀጠል የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ ሥርዓት ለመገንባት በሁሉም የልማት መስኮች ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ መሰረትም ሥራዎችን ለማሳለጥ የሚያግዙ በርካታ የሕግ ማዕቀፎች ተቀርፀው ተግባራዊ እየተደረጉ እንደሆነ እና ለውጦችም መታየት መጀመራቸውን አስረድተዋል።
በፌደራል፣ በክልል እና በከተሞች መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሰራር በላቀ ደረጃ መሻሻል እያሳየ መምጣቱን ጠቅሰው÷ ይህንን አጠናክሮ በማስቀጠል የዕድገትና የብልጽግናውን ዕቅድ ለማሳካት መረባረብ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ፎረሙ ከተሞችና አጋሮቻቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎቻቸውን በማስተዋወቅ እውቅና እንዲያገኙና ተሞክሮዎቻቸውን እንዲለዋወጡ ሚናው ጉልህ ነው ብለዋል፡፡
በመካከላቸው ጤናማ የውድድር መንፈስ እንዲኖር በማድረግ ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከተሞች ያላቸውን የገቢ አመራጮች በአግባቡ በመለየትና መሰብሰብ የሕብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ጠንክሮ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡
የከተሞችን የምግብ ዋስትና ችግሮችን ለመፍታት ተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡