ብልጽግና ፓርቲ ኮሮናን ለሚያክሙ የህክምና ባለሙያዎች መገልገያ የሚውሉ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ኮሮናን ለሚያክሙ የህክምና ባለሙያዎች መገልገያ የሚውሉ ቁሳቁሶችን ለአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ድጋፍ አደረገ፡፡
ድጋፎቹ የኮሮና ወረርሽኝ ህክምና ላይ የተሰማሩ የህክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን የሚከላከሉበት ሙሉ ሰውነት የሚሸፍን 500 ልብስና 8 ሺህ ጓንቶች ናቸው፡፡
የብልጽግና ዋና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም ዛሬ በተደረገው የርክክብ ስነ ስርዓት ወቅት እንዳሉት፣ የህክምና ባለሙያዎቻችን ትውልድና ታሪክ የማይረሳ ገድል እየፈጸሙ ነው፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ በሃገሪቱ ከተከሰተበት ወቅት አንስቶ የግል ህይወቴንና ቤተሰቤን ሳይሉ ሁሉ ነገራቸውንና ሙሉ ትኩረታቸውን የሌሎችን ህይወት ማዳን ላይ አድርገዋልም ብለዋል፡፡
የዛሬው ድጋፍም ከጎናቸው መሆናችንን ለማሳየትና ለሚሰሩት ስራ ያለንን አድናቆት ለመግለጽ ነው ያሉት ሃላፊው ሁሉም ህብረተሰብ ከጎናቸው ሆኖ እንዲያበረታታቸውና የድርሻውን እየተወጣ እንዲያግዛቸው ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዮሃንስ ጫላ በበኩላቸው ሥጦታው ትልቅ የአጋርነት መግለጫና ማበረታቻ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ወረርሽኝ ወቅት በቅንነት ህዝቡን ለማገልገል ያላቸውን ዝግጁነት ማረጋገጣቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡