ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ በማህበራዊ ልማት የምታደርገውን ድጋፍ ታጠናክራለች – አምባሳደር አሌክሲስ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ በትምህርትና ጤና ዘርፍ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች አሉ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክን፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ከአምባሳደር አሌክሲስ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
አፈ ጉባዔው በዚህ ወቅት ÷ በኢትዮጵያና ፈረንሳይና መካከል ያለው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የፈረንሳይ መንግሥት በትምህርት፣ ጤናና ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የሁለትዮሸ ግንኙነት ከአሁናዊው ሁኔታ አንጻር መቃኘት እንዳለበት አብራርተዋል፡፡
የፌዴሬሽን ም/ቤት ከፈረንሳይ የላይኛው ም/ቤት ጋር ያለው ግንኙነት በአዲስ መልክ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ፍላጎት እንዳላቸውም አንስተዋል፡፡
አምባሳደር አሌክሲስ በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ ለፈረሳይ ሕዝብ እና መንግሥት ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን አመልክተዋል፡፡
ፈረንሳይ በትምህርትና ጤና የምታደርገውን ድጋፍ እንዲሁም በቅርስ ጥገና የተደረሰውን ስምምነት ከግብ ለማድረስ እንደምትሰራ ማረጋገጣቸውን የም/ቤቱ ጽ/ቤት የኮሙኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ተረፈ በዳዳ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናክራ እንደምትቀጥልና በባለብዙ ወገን ግንኙነቶች የኢትዮጵያ ፍላጎት እንዲሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል፡፡