በኦሮሚያ ክልል የተፈጥሮ እና የሰው ሀብትን በማቀናጀት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አወሉ አብዲ በክልሉ የተፈጥሮ እና የሰው ሀብትን በማቀናጀት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው አሉ።
በዛሬው እለት በክልሉ ጅማ ዞን ዴዶ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናውኗል።
አቶ አወሉ አብዲ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በ2018 ምርት ዘመን በክልሉ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ይካሄዳል።
በቤተሰብና በሀገር ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ባለፉት ዓመታት በስንዴ ሰብል ኢኒሼቲቭ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
በሜካናይዜሽን እርሻ በመታገዝ አርሶ አደሩ ከባህላዊ እርሻ ተላቆ በዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎች በማረስ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዛሬው እለትም በጅማ ዞን ዴዶ ወረዳ ዋሮ ኮሎቦ ክላስተር 6ሺ 500 ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ መዝራት ተችሏል ብለዋል።
የጅማ ዞን አስተዳዳሪ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው፥ በዞኑ በበጋ ወቅት 513 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ እየለማ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ከድህነት ለመውጣት የስንዴ ልማት ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።
አርሶ አደሩ በ1 ሺህ 329 የእርሻ ትራክተርና በ12 ሺህ 220 የሞተር ውሃ ፓምፖች ታግዞ በመስኖ ልማቱ ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችል ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
በወርቅአፈራው ያለው