ቼልሲ ከባርሴሎና የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ…
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ 5ኛ ዙር መርሐ ግብር ቼልሲ በስታምፎርድ ብሪጅ ባርሴሎናን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
ጨዋታው ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት ላይ የሚጀምር ሲሆን፥ ሁለቱም ቡድኖች በሀገር ውስጥ ሊጎቻቸው ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በማሸነፍ ከድል መልስ የሚያደርጉት ተጠባቂ መርሐ ግብር ነው፡፡
በ4ኛ ዙር የሻምፒየንስ ሊግ መርሐ ግብር ቼልሲ ከካራባግ እንዲሁም ባርሴሎና ከክለብ ብሩጅ በተመሳሳይ አቻ የተለያዩ ሲሆን፥ የዛሬውን ጨዋታ ለማሸነፍ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ክለቦች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት 15 ጨዋታዎች ቼልሲ አምስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ያለው ሲሆን፥ ባርሴሎና ሦስት ጊዜ ማሸነፍ ችሏል፡፡
በሰባቱ ጨዋታዎች አቻ የተለያዩ ሲሆን፥ ባርሴሎና ወደ ለንደን ተጉዞ ቼልሲን በገጠመባቸው ያለፉት አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም፡፡
ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ ምሽት 2 ሰዓት ከ45 አያክስ አምስተርዳም ከቤኔፊካ፣ ጋላታሳራይ ከኡኒየን ሴንት ጊሎሴ ይገናኛሉ፡፡
ማንቼስተር ሲቲ ከባየር ሊቨርኩሰን፣ ማርሴይ ከኒውካስል ዩናይትድ፣ ናፖሊ ከካራባግ፣ ቦዶ ግሊምት ከጁቬንቱስ፣ ቦሩሺያ ዶርትመንድ ከቪያሪያል እንዲሁም ስላቪያ ፕራግ ከአትሌቲክ ቢልባኦ ምሽት 5 ሰዓት ላይ የሚደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች ናቸው፡፡
በአቤል ነዋይ