ውጤታማ የልማት ስራዎችን ለማስፋት የአመራሩ ተሞክሮ መቅሰም …
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ስድስት ማዕከላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሲወስዱ የቆዩ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
አመራሮቹ ባለፉት ቀናት “በመደመር መንግሥት እይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሃሳብ በ2ኛ ዙር የተሰጠውን ሥልጠና ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም በአዳማ ከተማ የነበሩ ሰልጣኞች በምሥራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ የገጠር ሞዴል ቀበሌንና ዘመናዊ የዓሣ እርባታ ማዕከልን፣ በቦራ ወረዳ የፓፓያና ሙዝ ልማት ክላስተር እንዲሁም በገላን ከተማ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።
በተመሳሳይ መልኩ የሻሸመኔ ማዕከል ሰልጣኞች በምዕራብ አርሲ ዞን ቆሬ ወረዳ የቢራ ገብስ ልማትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
እንዲሁም በነቀምቴ ክላስተር የቆዩ ሰልጣኞች የነቀምቴ ኢንዱስትሪ ፓርክን፣ የነቀምቴ ከተማ ኮሪደር ልማት እና የሶርጋ የወንዝ ዳርቻ ልማት ግንባታ ሒደትን ጎብኝተዋል፡፡
የማያ ክላስተር አመራር ሰልጣኞችም በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ባቢሌ እና ጉርሱም ወረዳዎች የማንጎ፣ ፓፓያ ፣ ሙዝ፣ የወተት ላሞች እርባታ እና በባቢሌ ከተማ የዶሮ እርባታ ክላስተር እና የተለያዩ የቱሪዝም ልማት ኮሪደሮችን ተመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል በጅማ እና ቡሌ ሆራ የሚገኙ ሰልጣኞች በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የተከናወኑ የተለያዩ ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
ጉብኝቱ ውጤታማ የልማት ስራዎችን ለማስፋት አመራሩ ተሞክሮ የሚቀስምባቸው እንደሆኑም ተመላክቷል።