የአንድ ቋት መጠጥ ውሃና ስነ-ንፅህና ብሔራዊ መርሃ ግብር የ2012 አፈጻጸም ተገመገመ
አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጀመሪያና ሁለተኛ ዙር የአንድ ቋት መጠጥ ውሃና ስነ-ንፅህና ብሔራዊ መርሃ ግብር (One Wash National Program) የ2012 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡
በውይይቱ በአንድ ቋት መጠጥ ውሃና ስነ-ንፅህና መርሃ ግብር በመጀመሪያው ዙር ተጨማሪ ጊዜና በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ዓመት የተሠሩ ሥራዎች ሪፖርትና የ2013 በጀት ዓመት ዕቅድ በውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡
መርሃ ግብሩ የመጀመሪያው ዙር በ438 ነጥብ 7 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በጀት በ382 የገጠር ወረዳዎች 17 ሺህ 335 የውሃ ተቋማት ግንባታና እድሳት በማከናወን 1 ነጥብ 9 ሚሊየን መጸዳጃ ቤቶችን በማስገንባት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
የተቋማት የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ስነ-ንፅህናን በሚመለከትም በትምህርት ቤቶች 1 ሺህ 756 የውሃ ፣ 3 ሺህ 440 የመጸዳጃ ቤቶች፣ በጤና ጣቢያዎች ደግሞ 1 ሺህ 920 የውሃ ተቋማት፣ 3 ሺህ 108 መጸዳጃ ቤቶች መገንባት መቻሉ ተጠቁሟል፡፡
በውይይቱ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ መንግሥት ለመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ለስነ-ንፅህና ዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት በዚህ ዓመት 2 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት መያዙን ገልጸዋል፡፡
በአንድ ቋት መጠጥ ውሃና ስነ-ንፅህና መርሃ ግብር ትኩረት ሰጥቶ በ2012 በጀት ዓመት የታዩ መዘግየቶችን በማካካስ፣ የዚህን ዓመት ዕቅድ በአግባቡ በመፈጸም ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ተግቶ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
መርሃ ግብሩ ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ የሆነ ሲሆን፥ እስከ አውሮፓውያኑ ሐምሌ 2024 የሚተገበር ነው ተብሏል፡፡
በዚህ መርሐ ግብር በ5 ዓመታት ውስጥ በ67 ከተሞች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማትን የመጠጥ ውሃና ስነ-ንፅህና አቅርቦት ላይ የሚሠራ መሆኑ መገለፁን ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡