የኢትዮ-ህንድ የትስስር ታሪክ ወሳኝ ምዕራፍ ወደፊት የሚቀጥል ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ረጅም እና ጥልቅ የሆነው የኢትዮጵያ እና ህንድ የትስስር ታሪክ ወሳኝ የጉዞ ምዕራፍ ወደፊት የሚቀጥል ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል የክብር እራት ግብዣ አድርገዋል።
በእራት ግብዣ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፤ እድገት የሚወረስ ሳይሆን በዓላማ፣ በጽናት እና በአጋርነት የሚገነባ ነው ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተሻገረ ክስተት መሆኑን ገልጸዋል።
ጉብኝቱ ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ እና በደፋር ሀሳቦች ለውጥን ማራመድ እንደሚችሉ የተረዱ የሁለት ሀገራት መሰባሰብ እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህም ረጅም እና ጥልቅ የሆነው የኢትዮጵያ እና ህንድ የትስስር ታሪክ ወሳኝ የሆነው የትብብር ጉዞ ምዕራፍ ወደፊት የሚቀጥል መሆኑን ማሳያ እንደሆነ አስረድተዋል።
እንደ ህንድ ጥንካሬያችንን በሀገር ውስጥ በመገንባት፣ ነፃነትን በጠበቀ መንገድ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ እናምናለን ብለዋል።
በተግባራዊ አስተዳደር እና ሰፊ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ላይ የተመሰረተው የህንድ ራዕይ ከመደመር ፍልስፍና ጋር የተጣጣመ እንደሆነም ተናግረዋል።
በጋራ ስንሰራ ጥንካሬያችንን ማብዛት እንችላለን የሚለው አመለካከት ዕድሎችን የሚከፍት ነው ሲሉ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ እና ህንድ አሳታፊ ልማትን በመደገፍ፣ በመከባበር ላይ የተመሰረተ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ትብብር እንዳላቸው አስታውሰው፤ ትብብሩ ለደቡብ ደቡብ አጋርነት አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጉብኝትም ይህንን የሚያጠናክር እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በዮናስ ጌትነት