Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድሬዳዋ ያስገነባቸውን ቤቶች ለአቅመ ደካሞች አስተላለፈ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በድሬዳዋ ያስገነባቸውን 20 ቤቶች ለአቅመ ደካማ ወገኖች አስተላልፏል።
ሚኒስቴሩ ቤቶቹን ለአቅመ ደካማ ወገኖች ባስረከበበት ሥነ ሥርዓት ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ሚኒስቴሩ ያስገነባቸው ቤቶች ዘመናዊ ተገጣጣሚ መሆናቸው ተገልጿል።
ሚኒስቴሩ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሰል ሰው ተኮር ስራዎችን አጠናክሮ የሚያስቀጥል መሆኑም ተመላክቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ እንደሀገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከናወኑ የሚገኙ በጎ ፍቃድ አገልግሎቶች የብዙዎችን የዘመሙ ጎጆዎች እንዲቃኑና ተስፋቸው እንዲለመልም አድርጓል።
ሚኒስቴሩ ለአቅመ ደካማ ቤተሰብ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ፣ በአረንጓዴ አሻራ እንዲሁም የቤት ግንባታና እድሳትን ጨምሮ የተለያዩ የበጎ ፍቃድ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወቅትን ጠብቆ ከማድረግ ይልቅ የዘወትር ተግባር ማድረግ ይገባል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው፥ መንግስት በርካታ ሰው ተኮር ተግባራትን በማከናወን የዜጎች ህይወት እንዲሻሻል እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በከተማዋ ተገንብተው በዛሬው ዕለት ለአቅመ ደካማ ወገኖች የተላለፉት ምቹ ቤቶች ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸው፥ በከተማ አስተዳደሩ ህዝብና መንግስት ስም አመስግነዋል።
በተስፋዬ ኃይሉ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.