የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ወጣቶች የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል – ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ
አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 15 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ወጣቶች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።
ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በጤና ሚኒስቴር በተዘጋጀው የወጣቶች ጤና መድረክ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፕሬዚዳንቷ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ወጣቶች ከምንም በፊት አካላዊና አዕምሯዊ ጤናቸውን መጠበቅ ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው።
“ጤናማ ትውልድ ከሌለ ሃገር ጤና አትውልም፣ አታድርም” ያሉት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ሃገሪቱ ከተጋረጠባት ወረርሽኝ ልትወጣ የምትችለው በወጣቶች ጠንካራ ትግል ነው ብለዋል።
ከዚህ አንጻርም ወጣቶች ራሳቸውን ከወረርሽኙ በመጠበቅና ለማህበረሰቡ ስለወረርሽኙ ተገቢውን ትምህርት በመስጠት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባልም ነው ያሉት።
ወጣቶች አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር ዝግጁ እስከሆኑ ድረስ የነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለች እንደምትሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ወጣቶች ህልማቸው ከአድማስ ወዲያ የሚሻገር መሆን እንዳለበትና የሰላም ጠበቃና የልማት አውራ መሆን እንደሚጠበቅባቸውም አውስተዋል፡፡
መንግሥት የወጣቶችን በተለይም ደግሞ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የወጡ ፖሊሲዎችና ስትሬቴጂዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዚህ ዓመት ባጸደቀው የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ የወጣቶች ጤና ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህ ዓመት በሚኒስቴሩ ወጣቶችና የአፍላ ወጣቶችን ጤና የሚከታተል አዲስ ቡድን መቋቋሙንም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ የተጋረጠውን የኮሮናቫይረስ ለመከላከል በተለይ ወጣቶች የበኩላቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።