የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አካታችነትን ለማረጋገጥ በዲጂታል ክህሎት ላይ በትኩረት ይሰራል
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን አካታችነት ለማረጋገጥ በዲጂታል ክህሎት ላይ በትኩረት ይሰራል አለ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ከቀናት በፊት በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉቀን ቀሬ እንዳሉት፥ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አካታችነትን ከማረጋገጥ አኳያ በተለይም በገጠር አካባቢዎች የሚኖረውን የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ያደረገ እንዲሆን በትኩረት ይሰራል፡፡
ለዚህም ስትራቴጂው በኢትዮጵያ እየተተገበሩ ከሚገኙ ሌሎች የገጠር ልማት ስትራቴጂዎች ጋር በማቀናጀት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ በሚያስችል መንገድ ተግባራዊ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
በዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ላይ የሚከናወኑ ተግባራት በሚፈለገው ልክ ውጤታማ እንዲሆኑ ዜጎች በዲጂታል ስርዓት ላይ ያላቸውን ግንዛቤና ክህሎት ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህንን ታሳቢ በማድረግ የስትራቴጂውን አካታችነት ለማረጋገጥ መንግስት የዜጎችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ